የአላህ መልክተኛ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- መጀመሪያ ወሕይ ወደርሳቸው መውረድ የጀመረው በእንቅልፋቸው የሚያዩት መልካም ህልም ነበር።

የአላህ መልክተኛ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- መጀመሪያ ወሕይ ወደርሳቸው መውረድ የጀመረው በእንቅልፋቸው የሚያዩት መልካም ህልም ነበር።

ከአማኞች እናት ዓኢሻ ረዲየሏሁ ዐንሃ - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - እንደተላለፈው እንዲህ አለች: «የአላህ መልክተኛ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- መጀመሪያ ወሕይ ወደርሳቸው መውረድ የጀመረው በእንቅልፋቸው የሚያዩት መልካም ህልም ነበር። ንጋት ብርሃን (እንደተፍለቅላቂ ጎህ) በገሃዱ አለም የሚከሰት ቢሆን እንጂ አንድም ህልም አያዩም ነበር። ከዚያም ከሰዎች መገለል እርሳቸው ዘንድ ተወዳጅ ሆነ። በሒራ ዋሻም ከሰዎች ተገልለው ወደ ቤተሰባቸው ሳይመለሱ በርካታ ቀናቶችን አላህን እያመለኩ ያሳልፉ ነበር። ለዚህም ስንቅ ይዘው ነበር የሚወጡት። ከዛም ወደ ኸዲጃ ተመልሰው ለተመሳሳይ ድርጊት ስንቅ ይዘው ይወጡ ነበር። ይህንንም በሒራ ዋሻ ሳሉ እውነት ወደርሳቸው እስኪመጣ ድረስ ቀጠሉበት። መልአኩ ወደርሳቸው መጣና "አንብብ!" አላቸው። (ያኔ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልፁታል) እኔም "ማንበብ አልችልም!" አልኩት። እንዲህም አሉ "ጭንቅ እስኪለኝ ድረስ ይዞ ጨመቀኝና ለቀቀኝ።" አሁንም "አንብብ!" አለኝ። እኔም "ማንበብ አልችልም።" አልኩት። "አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ይዞኝ ጭንቅ እስኪለኝ ድረስ ጨመቀኝና ለቀቀኝ።" አሁንም "አንብብ!" አለኝ። እኔም "ማንበብ አልችልም።" አልኩት። "አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ይዞ ጭንቅ እስኪለኝ ድረስ ጨመቀኝና ለቀቀኝ።" መልአኩም እንዲህ አለኝ: {አንብብ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም) አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲሆን} [አልዐለቅ: 1 - 3] የአላህ መልክተኛ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- እነዚህን አንቀጾች ሸምድደው ልባቸው እየተንቀጠቀጠ ተመለሱ። ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ ረዲየሏሁ ዐንሃ - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - ዘንድም በመግባት "አከናንቡኝ! አከናንቡኝ!" አሉ። ድንጋጤው እስኪወገድላቸው ድረስም አከናነቧቸው። ለኸዲጃም ጉዳዩን ነገሯቸው። "ለነፍሴ ፈርቻለሁ።" አሉ። ኸዲጃም እንዲህ አለቻቸው "(እንደዚህ ከማሰብ) ተከልከል! በአላህ እምላለሁ! ከቶም አላህ አይተውህም። አንተ ዝምድና ትቀጥላለህ፤ ለደካሞች ትረዳለህ፤ ለተቸገሩ ትሰጣለህ፤ እንግዳ ታከብራለህ፤ እውነተኛ ጉዳዮች ላይ ትተባበራለህ።" እርሳቸውንም ይዛ የአጎቷ ልጅ ወደሆነው ወረቃ ቢን ነውፈል ቢን አሰድ ቢን ዐብዲል ዑዛ ዘንድ ሄደች። በጃሂሊያ ዘመን ክርስቲያን የሆነ ሰው ነበር። መጽሐፍን በዕብራይስጠኛ ይፅፍ ነበር። አላህ እንዲፅፍ የሻለትን ያህልም ኢንጂልን በዕብራይስጠኛ ይፅፍ ነበር። አይኑ የታወረ እጅግ የጃጀ ሽማግሌ ነበር። ኸዲጃም ለርሱ "የአጎቴ ልጅ ሆይ! እስኪ የወንድምህ ልጅ የሚለውን ስማ።" አለችው። ወረቃም ለርሳቸው "የወንድሜ ልጅ ሆይ! ምንድን ነው የምታየው?" አላቸው። የአላህ መልክተኛም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- የተመለከቱትን ነገሩት። ወረቃም ለርሳቸው "ይህ አላህ በሙሳ ላይ ያወረደው ናሙስ ነው። ህዝቦችህ ከሀገርህ በሚያስወጡህ ጊዜ ዋ ምኞቴ! ምነው ያኔ ጠንካራ ወጣት በሆንኩ! ዋ ምኞቴ በህይወት በኖርኩ!" አላቸው። የአላህ መልክተኛም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- "እነርሱ ያስወጡኛልን?" አሉ። እርሱም "አዎን አንተ ይዘኸው የመጣኸውን አምሳያ ይዞ የመጣ አንድም ሰው የለም ጠላት ተደርጎ የተያዘ ቢሆን እንጂ፤ የመልክተኝነት ዘመንህ ላይ ከደረስኩ ጠንካራ እርዳታን እረዳሀለሁ።" አላቸው። ከዚያም ግን ወረቃ ብዙም ሳይቆይ አረፈ። ወሕዩም ተቋረጠ።»

[ሶሒሕ ነው።] [ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።]

الشرح

የአማኞች እናት ዓኢሻ ረዺየሏሁ ዐንሃ - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - እንዲህ በማለት ስለ ወሕይ አጀማመር ተናገረች: "የአላህ መልክተኛ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- መጀመሪያ ወሕይ ወደርሳቸው መውረድ የጀመረው በእንቅልፋቸው መልካም ህልም በማየት ነበር። በእንቅልፋቸው አንድም ህልም አያዩም ነበር እንደ ንጋት ብርሃን በሚመስል መልኩ በግልፅ የሚከሰት ቢሆን እንጂ። ቀጥሎ እርሳቸው ዘንድ ከሰዎች መገለል ተወዳጅ ሆነ። በሒራ ዋሻም ከሰዎች ተገልለው ወደ ቤተሰባቸው ሳይመለሱ በርካታ ቀናቶችን አላህን ሲያመልኩ ያሳልፉ ነበር። ለዚህም ስንቅ ይዘው ነበር የሚወጡት። ቀጥለው ወደ አማኞች እናት ኸዲጃ ረዲየሏሁ ዓንሃ -አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና- በመመለስ ለተመሳሳይ ድርጊት ስንቅ ይዘው ይወጡ ነበር። ይህንን ማድረጋቸውንም በሒራ ዋሻ ሳሉ እውነት ወደርሳቸው እስኪመጣ ድረስ ቀጠሉበት። መልአኩ ጂብሪልም ዐለይሂ ሰላም ወደርሳቸው በመምጣት "አንብብ" አላቸው። ነቢዩም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- "ማንበብ አልችልም።" አሉ። እንዲህም አሉ: ጭንቅ ጥብብ እስኪለኝና እስኪሳነኝ ድረስ ጭምቅ አደረገኝ። ከዚያም ለቀቀኝና "አንብብ" አለኝ። እኔም "ማንበብ አልችልም።" አልኩት። አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ጭንቅ ጥብብ እስኪለኝና እስኪሳነኝ ድረስ ጭምቅ አደረገኝ። ከዚያም ለቀቀኝና "አንብብ" አለኝ። እኔም "ማንበብ አልችልም።" አልኩት። አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ጭንቅ ጥብብ እስኪለኝና እስኪሳነኝ ድረስ ጭምቅ አደረገኝና እንዲህ አለኝ: {አንብብ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም* ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)* አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲሆን} [አልዐለቅ: 1 - 3] ነቢዩም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- አንቀጾቹን ሸምድደው ሞትን ፈርተው ልባቸው እየተንቀጠቀጠ ተመለሱ። የአማኞች እናት ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ ረዲየሏሁ ዓንሃ - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - ዘንድም በመግባት እንዲህ አሉ: "በልብስ ጠቅልሉኝ! በልብስ ጠቅልሉኝ!" ፍርሃት እስኪለቃቸው ድረስም በልብስ ጠቀለሏቸው። ለኸዲጃም ጉዳዩን ነገሯትና እንዲህ አሉ: "ሞትን በነፍሴ ላይ ፈርቻለሁ።" ኸዲጃም እንዲህ አለች: "ይህንን ከመናገር ተከልከል! በአላህ እምላለሁ! አላህ በፍፁም አይተውህም። አንተ ዝምድናን ትቀጥላለህ፤ ራሱን ያልቻለን ደካማ ታግዛለህ፤ ሰዎች ካንተ ውጪ ማንም ዘንድ በማያገኙት መልኩ በመስጠት ምንም የሌለውን ድሃ ትረዳለህ፤ እንግዳን ታከብራለህ፤ ትክክለኛ ጉዳዮች ላይ ትተባበራለህ።" ኸዲጃም እርሳቸውን ይዛ የአጎቷ ልጅ ወደሆነው ወረቃ ቢን ነውፈል ቢን አሰድ ቢን ዐብዲል ዑዛ ዘንድ ሄደች። በጃሂሊያ ዘመን የጃሂሊዮችን እምነት በመተው ክርስቲያን የሆነ ሰው ነበር። አላህ እንዲፅፍ የሻለትን ያህልም ኢንጂልን በዕብራይስጠኛ ይፅፍ ነበር። አይኑ የታወረ እጅግ የጃጀ ሽማግሌ ነበር። ኸዲጃም ለርሱ እንዲህ አለች: "የአጎቴ ልጅ ሆይ! እስኪ የወንድምህ ልጅ የሚለውን ስማ።" ወረቃም ለርሳቸው "የወንድሜ ልጅ ሆይ! ምንድን ነው የምታየው?" አላቸው። የአላህ መልክተኛም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- የተመለከቱትን ነገሩት። ወረቃም ለርሳቸው "ይህ አላህ በሙሳ ላይ ያወረደው ጂብሪል ነው። ህዝቦችህ ከሀገርህ በሚያስወጡህ ጊዜ ዋ ምኞቴ! ጠንካራ ወጣት በሆንኩ! ዋ ምኞቴ በህይወትም በኖርኩ!" አላቸው። የአላህ መልክተኛም ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- "እነርሱ ያስወጡኛልን?" አሉ። እርሱም "አዎን አንተ ይዘኸው የመጣኸውን አምሳያ ይዞ የመጣ አንድም ሰው የለም ጠላት ተደርጎ የተያዘና ጉዳት የደረሰበት ቢሆን እንጂ፤ የመልክተኝነት ዘመንህ ላይ ከደረስኩ ጠንካራ እርዳታን እረዳሀለሁ።" አላቸው። ከዚያም ግን ወረቃ ብዙም ሳይቆይ አረፈ። ወሕዩም ለተወሰነ ጊዜ ዘገየ።

فوائد الحديث

ወሕይ ወደ ነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- የጀመረበት ሁኔታ መገለፁን እንረዳለን።

የነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ህልም ከወሕይ ክፍሎች መካከል አንዱ እንደሆነ እንረዳለን።

ስንቅ መያዝ የተደነገገ እንደሆነና ከተወኩል ጋር እንደማይጋጭ እንረዳለን። በአላህ ከሚመኩ ሰዎች ባጠቃላይ በላጭ የሆኑት ነቢዩ ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ሳይቀሩ ስንቅ ይዘዋልና።

አላህ ሱብሓነሁ ወተዓላ ባሮቹ ያላወቁትን ማሳወቁና ከመሃይምነት ፅልመት ወደ እውቀት ብርሃን ማሸጋገሩ የርሱ ቸርነት የተሟላ መሆኑን ያስረዳናል።

የጽሑፍ እውቀት ያለውን ደረጃ እንረዳለን። ይህም ተቆጥረው የማያልቁ ትላልቅ ፋይዳዎች ስላሉት ነው። በጽሑፍ እውቀቶች ተሰንደዋል፤ ፍርዶች ተወስነው ተቀመጠዋል፤ የቀደምቶች ንግግር ተጠብቀው ተይዘዋል፤ አላህ ያወረደው መጽሐፍ ተጠበቋል፤ የዲንና የዱንያ ጉዳዮች ተስተካክለዋል።

ከቁርአን መጀመሪያ የወረደው {አንብብ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም} [አልዐለቅ:1] የሚለው አንቀፅ እንደሆነ እንረዳለን።

መልካም ስነምግባርና መልካም ስብእናን መላበስ ከተለያዩ መጥፎ አደጋዎችና ከጎጂ ነገሮች ለመዳን ምክንያት ነው። መልካሙ የበዛ ሰው ፍፃሜው ያምርለታል። የዲንና የዱንያ ደህንነትም ተስፋ ይደረግለታል።

ሰውን ፊትለፊቱ ማሞገስ የሚያመጣው ጥቅም ካለ እንደሚፈቀድ እንረዳለን።

አስፈሪ ነገር የተከሰተበትን ሰው ማፅናናትና ማበሰር፤ እንዲሁም ከዛ ነገር የሚገላገልበትን መንገድ ማውሳት ይገባል።

ይህ ሐዲሥ የኸዲጃን ረዺየሏሁ ዐንሃ - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - ምሉዕነት፣ የአመለካከቷን ግዝፈት፣ የመንፈስ ጥንካሬዋን፣ የግንዛቤዋን ትልቅነት በደንብ የሚያስረዳ ጥግ የደረሰ ማስረጃ ነው። ነቢዩን ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም -የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና- ስትገልፅ ሁሉንም የመልካምነት መሰረትና አንኳር ጉዳዮችን አወሳች። መልካምነት ወይ ለቅርብ ዘመዶች ነው ወይም ለባዳ ነው፤ ወይ በሰውነት ነው ወይም በገንዘብ ነው፤ ወይ ራሱን ለቻለ ነው ወይም ራሱን ላልቻለ ነው። ኸዲጃም መናገር ባለባት ቦታ ተገቢውን ንግግር ሰፋ አድርጋ ተናገረች።

አንድ ጉዳይ የተከሰተበት ሰው ምክሩን ለሚተማመንበትና ሃሳቡ እውነትን ለሚገጥም ሰው ማሳወቁ ይወደዳል።

التصنيفات

Prophet's Lineage