ከናንተ በፊት ከነበሩት ህዝቦች መካከል አንድ ንጉስ ነበር። ለርሱም ጠንቋይ ነበረው።

ከናንተ በፊት ከነበሩት ህዝቦች መካከል አንድ ንጉስ ነበር። ለርሱም ጠንቋይ ነበረው።

ከሱሀይብ - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል፦ «ከናንተ በፊት ከነበሩት ህዝቦች መካከል አንድ ንጉስ ነበር። ለርሱም ጠንቋይ ነበረው። (ጠንቋዩ) ያረጀ ጊዜም ለንጉሱ እንዲህ አለው: "እኔ አርጅቻለሁ። ጥንቆላ የማስተምረው አንድ ህፃን ልጅ ወደ እኔ ላክልኝ።" ንጉሱም የሚያስተምረውን ህፃን ልጅ ወደርሱ ላከለት። ልጁም ወደ ጠንቋዩ መንገድ ሲጀምር አንድ ባህታዊ ይመለከታል። እርሱ ዘንድም ተቀምጦ ንግግሩን ያዳምጥና ያስደስተዋል። ዘውትር ወደ ጠንቋዩ ዘንድ ሲሄድ በባህታዊው በኩል ሲያልፍ ተቀምጦ አዳምጦ ይሄዳል። ጠንቋዩም (በማርፈዱ) ይመታዋል። ይህንንም ያጋጠመውን ቅሬታ ለባህታዊው ነገረው። ባህታዊውም: "ጠንቋዩ ይመታኛል ብለህ ከፈራህ ቤተሰቤ ነው ያዘገየኝ በለው። ቤተሰብህ ይመቱኛል ብለህ ከፈራህ ደሞ ጠንቋዩ ነው ያዘገየኝ በላቸው።" አለው። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለ አንድ ቀን በመንገዱ ሰዎች እንዳያልፉ መንገድ በዘጋ ትልቅ እንስሳ በኩል አለፈ። እንዲህም አለ: "ጠንቋዩ ነው ትክክለኛ ወይስ ባህታዊው ነው ትክክለኛ የሚለውን ዛሬ ማወቅ እችላለሁ።" ብሎ ድንጋይ አነሳና "አላህ ሆይ! ከጠንቋዩ እምነት ይልቅ የባህታዊው እምነት አንተ ዘንድ ተወዳጅ ከሆነ ሰዎች በመንገዳቸው ያልፉ ዘንድ ይህንን እንስሳ ግደል።" በማለት ወረወረውና ገደለው። ሰዎችም አለፉ። ይህንንም ለባህታዊው ነገረው። ባህታዊውም ይህንን ሲሰማ "ልጄ ሆይ! አንተ ዛሬ ከኔ የተሻልክ ሆነሃል። ጉዳይህ የማየውን ያህል ደርሷልና ትፈተናለህ። ፈተና ሲገጥምህም ወደ እኔ እንዳትጠቁም።" አለው። ልጁም እውሮችንና ለምጣሞችን ይፈውስ፤ ከተለያዩ በሽታዎችም ሰዎችን ያክም ነበር። ይህንንም ታውሮ የነበረ አንድ የንጉሱ አማካሪ ሰማና በርካታ ስጦታዎችን ሸክፎ ወደርሱ በመምጣት "ይህ ሰብስቤ ያመጣሁት ከፈወስከኝ ያንተ ይሆናል።" አለው። ልጁም "እኔ አንድንም ሰው አልፈውስም። የሚፈውሰው አላህ ነው። በአላህ ካመንክ አላህን እለምንልህና ትፈወሳለህ።" አለው። በአላህም አመነ አላህም ፈወሰው። ንጉሱም ዘንድ በመምጣት ከዚህ በፊት ይቀመጥ እንደነበረው ተቀመጠ። ንጉሱም ለርሱ: "አይንህን ማነው የመለሰልህ?" ብሎ ጠየቀው። አማካሪውም: "ጌታዬ" አለው። ንጉሱም: "ከኔ ውጪ ሌላ ጌታ አለህን?" አለው። አማካሪውም: "የኔም ያንተም ጌታ አላህ ነው።" በማለት መለሰለት። ልጁን እስኪጠቁም ድረስም ይዞት ከማሰቃየት አልተወገደም። ልጁም ተይዞ ቀረበ። ንጉሱም በመደነቅ "ልጄ ሆይ! ጥንቆላህ አይነ ስውራንና ለምጣሞችን እስከመፈወስ ደረሰ! ይህንን ሰራህ! ይህንን ሰራህ!" አለው። ልጁም: "እኔ አንድንም አልፈውስም። የሚፈውሰው አላህ ነው።" በማለት መለሰ። ይዞትም ባህታዊውን እስኪጠቁም ድረስ ልጁን ከማሰቃየት አልተወገደም። ባህታዊውም ተይዞ ቀረበ። ለርሱም "ከሃይማኖትህ ውጣ!" ተባለ። እርሱም "በፍፁም!" አለ። መጋዝ አስመጡናና አናቱ መሀል ላይ አስቀመጡት። ከዛም ሁለት ቦታ ከፍለው ጣሉት። ቀጥለው የንጉሱን አማካሪ አቀረቡት። ለርሱም "ከሃይማኖትህ ውጣ!" ተባለ። እርሱም "በፍፁም!" አለ። መጋዝ አናቱ መሀል ላይ አስቀመጠ። ከዛም ሁለት ቦታ ከፍሎ ጣለው። ቀጥለው ልጁን አቀረቡት። "ከሃይማኖትህ ውጣ!" ተባለ። እርሱም "በፍፁም!" አለ። ንጉሱም ልጁን ለተወሰኑ ወታደሮቹ ሰጠና "እርሱን እንዲህ እንዲህ ወደሚባል ተራራ ውሰዱትና ተራራው ላይ ይዛችሁት ውጡ። የተራራው ጫፍ ላይ ስትደርሱ ከሃይማኖትህ ውጣ በሉት። ከተቀበለ አምጡት ካልተቀበለ ወርውሩት።" አላቸው። እርሱንም ወደ ተራራው ይዘውት ወጡ። ልጁም "አላህ ሆይ! በፈለግከው መንገድ ከነርሱ ተንኮል ጠብቀኝ" አለ። ተራራው ተርገፈገፈና ወደቁ። ልጁም ወደ ንጉሱ መጣ። ንጉሱም ለልጁ "ወታደሮቹ ምን ሆኑ?" አለው። ልጁም "አላህ ከነርሱ ተንኮል ጠበቀኝ" አለው። ንጉሱም ለሌሎች ወታደሮች ልጁን ሰጠ። እንዲህም አላቸው: "ልጁን በጀልባ ጭናችሁ ውሰዱት። የባህሩ መሃል ስትደርሱ ከሃይማኖትህ ውጣ በሉት። ከተቀበለ አምጡት ካልተቀበለ ወደ ባህሩ ጣሉት።" ልጁንም ይዘውት ሄዱ። ልጁም "አላህ ሆይ! በፈለግከው መንገድ ከነርሱ ተንኮል ጠብቀኝ" አለ። ጀልባዋ ተገለበጠችና ሰመጡ። ልጁም ወደ ንጉሱ መጣ። ንጉሱም ለልጁ "ወታደሮቹ ምን ሆኑ?" አለው። ልጁም "አላህ ከነርሱ ተንኮል ጠበቀኝ" አለው። አክሎም "እኔ የማዝህን እስካልፈፀምክ ድረስ ልትገለኝ አትችልም" አለው። ንጉሱም: "ምንድነው እርሱ?" አለው። ልጁም "በቅድሚያ ሰዎችን አንድ ሰፊ ሜዳ ላይ ሰብስበህ የዘንባባ ግንድ ላይ ትሰቅለኛለህ። ቀጥሎ ከሰገባዬ ቀስት ትውስዳለህ። ቀጥሎ ቀስቱን ከደጋኑ መሃል ካደረግክ በኋላ "የዚህ ልጅ ጌታ በሆነው በአላህ ስም እወረውራለሁ።" በል። ከዛም ወርውረው። አንተ ይህንን ካደረግክ ትገለኛለህ።" አለው። ንጉሱም ሰዎችን አንድ ሰፊ ሜዳ ላይ ሰበሰበና ልጁን የዘንባባ ግንድ ላይ ሰቀለው። ቀጥሎ ከሰገባው ቀስቱን አወጣና ቀስቱን ደጋኑ መሃል ላይ ካደረገ በኋላ "የዚህ ልጅ ጌታ በሆነው በአላህ ስም እወረውራለሁ።" አለና ወረወረ። ቀስቷም ቅንጡ (ከጆሮው ጎን ያለ አጥንት) ላይ ተሰካች። ልጁም ቀስቱ ያረፈችበትን የጆሮውን ጎን እንደያዘ ሞተ። ሰዎችም "በልጁ ጌታ አምነናል። በልጁ ጌታ አምነናል። በልጁ ጌታ አምነናል።" አሉ። ንጉሱም ጋር በመምጣት እየማሉ "ያ የምትፈራው ነገር ተከሰተብህ አይደል? የምትፈራው ደረሱ፤ ሰዎች አመኑ።" ተባለ። ንጉሱም በመንገድ ዳር ዳር ጉድጓድ እንዲቆፈር አዘዘ። ጉድጓዱም ተቆፈረ። እሳትም ተቀጣጠለ። እንዲህም አለ: "ከሃይማኖቱ ለቆ ያልወጣን። እሳት ውስጥ አቃጥሉት። ወይም እሳት ውስጥ ግባ በሉት።" ህዝቡ ሁሉ አንዲት ህፃን ልጅ የተሸከመች ሴት እስክትቀር ድረስ ንጉሱ እንዳለው እሳት ውስጥ ገቡ። እሳት ውስጥ ለመግባት አመነታች። ያዘለችው ጨቅላ ግን "እናቴ ታገሺ አንቺ እውነት ላይ ነሽ።" አላት።»

[ሶሒሕ ነው።] [ሙስሊም ዘግበውታል።]

الشرح

ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለው ተናገሩ: ከእኛ በፊት ከነበሩት ህዝቦች መካከል አንድ ንጉስ ነበር። ለርሱም አንድ ጠንቋይ ነበረው። ጠንቋዩ ያረጀ ጊዜ ለንጉሱ እንዲህ አለው: "እኔ አርጅቻለሁ። ጥንቆላ የማስተምረውን ብላቴና ወደ እኔ ላክልኝ።" ንጉሱም የሚያስተምረውን ብላቴና ልጅ ወደርሱ ላከለት። ልጁ ወደ ጠንቋዩ መንገድ ሲጀምር መንገድ ላይ አንድ ባህታዊ ነበር። አንድ ቀን እርሱ ዘንድ ተቀምጦ ንግግሩን ያዳምጥና ያስደስተዋል። ዘወትር ወደ ጠንቋዩ ዘንድ ሲሄድ በባህታዊው በኩል ሲያልፍ ተቀምጦ አዳምጦ ይሄዳል። ጠንቋዩም (በማርፈዱ) ይመታዋል። ይህንንም ያጋጠመውን ቅሬታ ለባህታዊው ነገረው። ባህታዊውም: "ጠንቋዩ ይመታኛል ብለህ ከፈራህ ቤተሰቤ ነው ያዘገየኝ በለው። ቤተሰብህ ይመቱኛል ብለህ ከፈራህ ደሞ ጠንቋዩ ነው ያዘገየኝ በላቸው።" አለው። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለ አንድ ቀን ሰዎች እንዳያልፉ መንገድ በዘጋ ትልቅ እንስሳ በኩል አለፈ። እንዲህም አለ: "ዛሬ ጠንቋዩ ነው ትክክለኛ? ወይስ ባህታዊው ነው ትክክለኛ? የሚለውን አውቃለሁ።" ድንጋይም አነሳና "አላህ ሆይ! ከጠንቋዩ እምነት ይልቅ የባህታዊው እምነት አንተ ዘንድ ተወዳጅ ከሆነ ሰዎች በመንገዳቸው ያልፉ ዘንድ ይህንን እንስሳ ግደል።" በማለት ወረወረውና ገደለው። ሰዎችም አለፉ። ይህንንም ለባህታዊው ነገረው። ባህታዊውም ለርሱ እንዲህ አለው: "ልጄ ሆይ! አንተ ዛሬ ከኔ የተሻልክ ሆነሃል። ጉዳይህ የማየውን ያህል ደርሷልና ትፈተናለህ። ፈተና ሲያጋጥምህም ወደ እኔ እንዳትጠቁም።" አለው። ልጁም እውሮችንና ለምጣሞችን ይፈውስ ጀመር። በአላህ ፍቃድም ከተለያዩ በሽታዎችም ሰዎችን ያክም ነበር። ይህንንም ታውሮ የነበረ አንድ የንጉሱ አማካሪ ሰማና በርካታ ስጦታዎችን ሸክፎ ወደርሱ በመምጣት እንዲህ አለው: "ይህ ሰብስቤ ያመጣሁት ከፈወስከኝ ያንተ ይሆናል።" ልጁም "እኔ አንድንም ሰው አልፈውስም። የሚፈውሰው አላህ ነው። በአላህ ካመንክ አላህን እለምንልህና ትፈወሳለህ።" አለው። በአላህም አመነ አላህም ፈወሰው። ንጉሱም ዘንድ በመምጣት ከዚህ በፊት ይቀመጥ እንደነበረው ተቀመጠ። ንጉሱም ለርሱ: "አይንህን ማነው የመለሰልህ?" ብሎ ጠየቀው። አማካሪውም: "ጌታዬ" አለው። ንጉሱም: "ከኔ ውጪ ሌላ ጌታ አለህን?" አለው። አማካሪውም: የኔም ያንተም ጌታ አላህ ነው።" በማለት መለሰ። ልጁን እስኪጠቁም ድረስም ይዞት ከማሰቃየት አልተወገደም። ልጁም ተይዞ ቀረበ። ንጉሱም በመደነቅ እንዲህ አለው: "ልጄ ሆይ! ጥንቆላህ አይነ ስውራንና ለምጣሞችን እስከመፈወስ ደረሰ ማለት ነዋ! ይህንን ሰራህ! ይህንን ሰራህ!" ልጁም: "እኔ አንድንም አልፈውስም። የሚፈውሰው አላህ ነው።" በማለት መለሰ። ይዞትም ባህታዊውን እስኪጠቁም ድረስ ልጁን ከማሰቃየት አልተወገደም። ባህታዊውም ተይዞ ቀረበ። ለርሱም "ከሃይማኖትህ ውጣ!" ተባለ። እርሱም "በፍፁም!" አለ። መጋዝ አስጠሩና አናቱ መለያ ጋር አስቀመጡት። ከዛም ለሁለት ሰንጥቀው ጣሉት። ቀጥለውም የንጉሱን አማካሪ አቀረቡት። ለርሱም "ከሃይማኖትህ ውጣ!" ተባለ። እርሱም "በፍፁም!" አለ። መጋዝ አናቱ መለያ ጋር ተደረገና ለሁለት ተሰንጥቆ ወደቀ። ቀጥለውም ልጁን አቀረቡት። "ከሃይማኖትህ ውጣ!" ተባለ። እርሱም "በፍፁም!" አለ። ንጉሱም ልጁን ከሶስት እስከ አስር ለሚጠጉ ወታደሮቹ አሳልፎ ሰጠው። "እርሱን እንዲህ እንዲህ ወደሚባል ተራራ ውሰዱትና ተራራው ላይ ይዛችሁት ውጡ። የተራራው ጫፍ ላይ ስትደርሱ ከሃይማኖትህ ውጣ በሉት። ከተቀበለ አምጡት ካልተቀበለ ወርውሩት።" አላቸው። እርሱንም ወደ ተራራው ይዘውት ወጡ። ልጁም "አላህ ሆይ! በፈለግከው መንገድ ከነርሱ አንተው ብቃኝ።" አለ። ተራራው ተርገፈገፈ፣ ሀይለኛ መንቀጥቀጥ ተንቀጥቅጦ ወደቁ። ልጁም ወደ ንጉሱ መጣ። ንጉሱም ለልጁ "ወታደሮቹ ምን ሆኑ?" አለው። ልጁም "አላህ ከነርሱ ተንኮል ጠበቀኝ" አለ። ንጉሱም ለሌሎች ወታደሮች ልጁን ሰጠ። እንዲህም አላቸው: "ልጁን በጀልባ ጭናችሁ ውሰዱት። የባህሩ መሃል ስትደርሱ ከሃይማኖትህ ውጣ በሉት። ከተቀበለ አምጡት ካልተቀበለ ወደ ባህሩ ጣሉት።" ልጁንም ይዘውት ሄዱ። ልጁም "አላህ ሆይ! በፈለግከው መንገድ ከነርሱ ተንኮል ጠብቀኝ።" አለ። ጀልባዋ ተገለበጠችና ሰመጡ። ልጁም ወደ ንጉሱ መጣ። ንጉሱም ለልጁ "ወታደሮቹ ምን ሆኑ?" አለው። ልጁም "አላህ ከነርሱ ተንኮል ጠብቀኝ።" አለው። አክሎም "አንተ እኔ የማዝህን እስካልፈፀምክ ድረስ ልትገለኝ አትችልም።" አለው። ንጉሱም: "ምንድነው እርሱ?" አለው። ልጁም "በቅድሚያ ሰዎችን አንድ ገላጣ ሜዳ ላይ ሰብስበህ የዘንባባ ግንድ ላይ ትሰቅለኛለህ። ቀጥሎ ከሰገባዬ ቀስት ትውስዳለህ። ቀጥሎ ቀስቱን ከደጋኑ መሃል ካደረግክ በኋላ 'የዚህ ልጅ ጌታ በሆነው በአላህ ስም እወረውራለሁ።' በል። ከዛም ወርውረው። አንተ ይህንን ካደረግክ ትገለኛለህ።" አለው። ንጉሱም ሰዎችን አንድ ሜዳ ላይ ሰበሰበና ልጁን የዘንባባ ግንድ ላይ ሰቀለው። ቀጥሎ ከሰገባው ቀስቱን አወጣና ቀስቱን ደጋኑ መሃል ላይ ካደረገ በኋላ "የዚህ ልጅ ጌታ በሆነው በአላህ ስም እወረውራለሁ።" አለና ወረወረ። ቀስቷም በአይኑና በጆሮው መካከል ቅንጡ ላይ ተሰካች። ልጁም ቀስቱ ያረፈችበትን የጆሮውን ጎን እንደያዘ ሞተ። ሰዎችም "በልጁ ጌታ አምነናል። በልጁ ጌታ አምነናል። በልጁ ጌታ አምነናል።" አሉ። ንጉሱም ጋር በመምጣት "አየህ ያ የምትፈራውን ነገር? ያለ ጥርጥር ተከሰተብህ። ይሀውም ሰዎች ልጁን ተከትለው ሁሉም በጌታቸው አመኑ።" ተባለ። ንጉሱም በየመንገድ ዳር ዳር ትልቅና ረጃጅም ጉድጓድ እንዲቆፈር አዘዘ። ጉድጓዱም ተቆፈረ። እሳትም በውስጡ ተቀጣጠለ። እንዲህም አለ: "ከሃይማኖቱ ለቆ ያልወጣን። እሳት ውስጥ ጣሉትና አቃጥሉት።" ህዝቡ ሁሉ አንዲት ህፃን ልጅ የተሸከመች ሴት እስክትቀር ድረስ ንጉሱ እንዳለው እሳት ውስጥ ተወረወረ። እሳት ውስጥ ለመግባት አመነታች። ቦታዋን እንደያዘች ቆመች። እሳት ውስጥ መግባቱን ጠላች። ያዘለችው ጨቅላ ግን እንዲህ አላት: "እናቴ ታገሺ አንቺ እውነት ላይ ነሽ።"

فوائد الحديث

የወሊዮች (የአላህ ወዳጆች) ተዓምራት የተረጋገጠ መሆኑን እንረዳለን። ከነዚህም መካከል በልጁ ውርወራ ትልቅ እንስሳ መሞቱ፣ የልጁ ዱዓ ሁለት ጊዜ ተቀባይነት ማግኘቱና የሚጠባው ጨቅላ መናገሩ ይጠቀሳል።

በአላህ ላይ የተመካ ሰው በአላህ እንደሚረዳ እንረዳለን።

የትእግስትና በእምነት ላይ የመፅናት ደረጃ መገለፁን እንመለከታለን።

በለጋ እድሜ እውቀትን የመማርን ጥበብ እንረዳለን። በአብዛኛው የወጣትነት እድሜ ከእርጅና ዘመን በተሻለ ለፈጣን ሽምደዳ የተመቸ ነው።

ይህ ልጅ ከኢማኑ አለመራቁና አለመቀልበሱ የዚህ ልጅን የኢማን ጥንካሬ ያስረዳናል።

አላህ የተቸገረ ሰው ከለመነው እንደሚቀበል እንረዳለን።

አንድ ሰው ለአጠቃላዩ የሙስሊም ማህበረሰብ ጥቅም ሲባል ነፍሱን ለአደጋ ማጋለጥ እንደሚፈቀድለት እንረዳለን። ይህ ልጅ ለንጉሱ እንዴት እንደሚገለውና ነፍሱን የሚያጣበትን መንገድ ነገረው። እርሱም ከሰገባው ቀስት በመውሰድ በደጋኑ መሃል አድርጎት "የዚህ ልጅ ጌታ በሆነው በአላህ ስም እወረውራለሁ።" እንዲል መንገሩ ነው።

ጦርነትና መሰል ቦታዎች ላይ እንዲሁም ነፍስን ከጥፋት ለመታደግ መዋሸት እንደሚፈቀድ እንረዳለን።

አማኝ የሆነ ሰው ነፍሱን እስከማጣት ቢያደርሰው እንኳ በእምነቱ እውነተኝነትና እውነትን በመናገር ላይ በሚኖረው ፅናት ይፈተናል።

ወደ አላህ መንገድ ዳዕዋን ማድረግና እውነትን ማሰራጨት መስዋእትነት ያስከፍላል።

የሰዎች ቀልብ በአላህ እጅ ነው። አላህ የፈለገውን ይመራል። የፈለገውንም ያጠማል። ይህ ልጅ በጠንቋይ ታንፆና በመጥፎ የንጉስ እንክብካቤ ስር ሆኖም ቀናውን መንገድ ተመርቷል።

አንድ ሰው እውነታውን አውቆ እርግጠኝነት ላይ ለመድረስ የሚያስችለውን ምልክት እንዲያሳየው አላህን መጠየቅ ይፈቀድለታል።

የኢማን ባለቤቶች አላህ የሰጣቸውን ነገርና የቸራቸውን ነገር ባጠቃላይ ለሃይማኖቱ መገልገያና ወደርሱ መንገድ መስበኪያ ያውሉታል።

የጥፋት ምክንያቶች በአላህ እጅ ናቸው። ከፈለገ ተፈፃሚ ያደርጋታል። ከፈለገም ያቋርጣታል።

የክህደት ባለቤቶች ላለማመናቸው ምክንያት ማስረጃና መረጃ አንሷቸው አይደለም። የክህደታቸው ምክንያት እምቢተኝነትና ኩራት ነው።

ከአላህ ውጪ የሚመለኩና ግፈኞች እነርሱ ያሉበትን ተድላ ለማቆየት ሰዎችን ባጠቃላይ መግደልም የማይሰቀጥጣቸው እንደሆኑ እንረዳለን።

አላህ ግፈኞችን ካላሰቡበት ቦታ ይቀጣቸዋል። ሰዎች የልጁን ፅናት፣ የጥሪውን እውነተኝነትና በአላህ መንገድ የወቃሽን ወቀሳ እንደማይፈራ ሲመለከቱም በልጁ ጌታ አመኑ።

በዚህ ሐዲሥ መሰረት ከመሲሕ ዐለይሂ ሰላም ውጪ ገና አንቀልባ ላይ ሳሉ የተናገሩ እንዳሉ እንረዳለን። ይህ ሐዲሥ "ከሶስት ሰዎች በቀር በአንቀልባ ላይ ሆኖ የተናገረ የለም። ...." የሚለውን የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይስፈንና) ንግግር ያብራራል። እነዚህ ሶስቱ መጠቀሳቸውና በቁጥር መገደባቸው ከበኒ ኢስራኢል መካከል የሆኑትን ብቻ እንጂ ሌላውን አያካትትም።

التصنيفات

የዳዒዎች ታሪክና ግዴታቸው, ያለፉት ህዝቦች ሁኔታና ታሪክ